1 ነገሥት 1:30-36 NASV

30 ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በእኔም ምትክ በዙፋኔ ይቀመጣል’ ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር የማልሁልሽን ዛሬ በእውነት እፈጽማለሁ።”

31 ቤርሳቤህም ለጥ ብላ እጅ ከነሣች በኋላ፣ በንጉሡ ፊት ተንበርክካ፣ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ይኑር!” አለች።

32 ንጉሥ ዳዊትም፣ “ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። እነርሱም ንጉሡ ፊት በቀረቡ ጊዜ፣

33 እንዲህ አላቸው፤ “የጌታችሁን አገልጋዮች ይዛችሁ በመሄድ ልጄን ሰሎሞንን በራሴ በቅሎ ላይ አስቀምጡት፤ ወደ ግዮንም ይዛችሁት ውረዱ።

34 በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡት፤ ቀንደ መለከት ነፍታችሁም፣ ‘ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!’ ብላችሁ ጩኹ።

35 አጅባችሁት ወደ ላይ ውጡ፤ ከዚያም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፤ በእኔም ምትክ ይግዛ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ሾሜዋለሁ።”

36 የዮዳሄ ልጅ በናያስም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አሜን! የጌታዬ የንጉሡ አምላክ እግዚአብሔር ይህንኑ ያጽናው።