1 ነገሥት 1:43-49 NASV

43 ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ነገሩ ከቶ እንዲህ አይደለም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል።

44 ንጉሡ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን አብረውት እንዲሄዱ አድርጎአል፤ እነርሱም በንጉሡ በቅሎ አስቀመጡት።

45 ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ቀብተው አንግሠውታል። ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጥተዋል፤ ከተማዪቱም ይህንኑ አስተጋብታለች፤ እንግዲህ የሰማችሁት ድምፅ ይኸው ነው።

46 ከዚህም ሌላ ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።

47 የመንግሥቱ ሹማምትም ወደ ጌታችን ወደ ንጉሥ ዳዊት መጥተው፣ ‘አምላክህ የሰሎሞንን ስም ከአንተ ስም የላቀ፣ ዙፋኑንም ከአንተ ዙፋን የበለጠ ያድርገው’ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውለታል። ንጉሡም ዐልጋው ላይ ሆኖ በመስገድ፣

48 ‘ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን ወራሽ ዐይኔ እንዲያይ የፈቀደ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ምስጋና ይድረሰው’ አለ።”

49 በዚህም አዶንያስና የጠራቸው እንግዶች በሙሉ ደንግጠው ተነሡ፤ በየአቅጣጫውም ተበታተኑ።