1 ነገሥት 10:18-24 NASV

18 ከዚያም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው።

19 ዙፋኑ ባለ ስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል።

20 በስድስቱም ደረጃ ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ስድስት ስድስት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለም ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ከቶ ተሠርቶ አያውቅም።

21 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣበት ዋንጫ ሁሉ የወርቅ ሲሆን፣ የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ዕቃ በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበር፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ይህን ያህል ዋጋ ስላልነበረው፣ ከብር የተሠራ ዕቃ ፈጽሞ አልነበረም።

22 ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።

23 ንጉሥ ሰሎሞንም በሀብትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።

24 ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር።