1 ነገሥት 12:15-21 NASV

15 እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም የተናገረው ቀድሞውኑ እግዚአብሔር የወሰነው ስለ ሆነ፣ መፈጸም ነበረበትና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።

16 እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ ለንጉሡ እንዲህ በማለት መለሱ፤“ከዳዊት ምን ድርሻ አለን?ከእሴይስ ልጅ ምን የምናገኘው አለ?እስራኤል ሆይ፤ ወደየድንኳንህ ተመለስ፤ዳዊት ሆይ፤ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!ስለዚህም እስራኤላውያን ወደ ድንኳኖቻቸው ተመለሱ።

17 ሮብዓምም በይሁዳ ምድር በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ገዥ ሆነ።

18 ንጉሥ ሮብዓም የጒልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤል ሁሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።

19 ስለዚህ ሕዝቡ በዳዊት ቤት ላይ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳመፀ ነው።

20 ኢዮርብዓም መመለሱን እስራኤላውያን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ ወደ ጉባኤያቸው በማስጠራት በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት። ለዳዊት ቤት በታማኝነት ጸንቶ የተገኘው የይሁዳ ቤት ብቻ ነው።

21 ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልን ቤት ወግተው መንግሥቱን ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲመልሱ መላውን የይሁዳ ቤትና የብንያምን ነገድ ሰበሰበ፤ የሰራዊቱም ቊጥር አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ነበር።