21 ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዛት አልጠበቅህም፤
22 ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።
23 የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት።
24 ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር።
25 በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ።
26 ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን ሲሰማ፣ “ይህ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለለው ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ቃል መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ።
27 ከዚያም ነቢዩ ልጆቹን፣ “በሉ አህያ ጫኑልኝ” አላቸውና ጫኑለት።