1 ነገሥት 15:15-21 NASV

15 አባቱና እርሱ ለእግዚአብሔር የቀደሱትን ብርና ወርቅ እንዲሁም ዕቃዎችን አምጥቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት አስገባ።

16 አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

17 የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ይሁዳን ለመውጋት ወጣ፤ ከዚያም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት።

18 አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በታማኝ ሹማምቱ እጅ በደማስቆ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሀዳድ ላከው።

19 እንዲህም አለ፤ “በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ አሁንም በእኔና በአንተ መካከል ይኑር፤ እነሆ፣ የብርና የወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ወደ መጣበት እንዲመለስ፣ ሄደህ ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ።”

20 ቤንሀዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ጌንሳሬጥን በሙሉ ድል አደረገ።

21 ባኦስም ይህን ሲሰማ፣ በራማ የጀመረውን የምሽግ ሥራ አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ።