1 ነገሥት 16:9-15 NASV

9 ከሹማምቱ አንዱና የግማሽ ሠረገሎቹ አዛዥ የሆነው ዘምሪ ዐምፆ ተነሣበት፤ በዚያን ጊዜ ኤላ በቴርሳ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር፤

10 ዘምሪም ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነገሠ።

11 ዘምሪ ወዲያው እንደ ነገሠና በዙፋን እንደ ተቀመጠ፣ የባኦስን ቤተ ሰብ በሙሉ ገደለ፤ የሥጋ ዘመድም ሆነ ወዳጅ አንድም ወንድ አላስቀረም።

12 በዚህ ሁኔታም በነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የባኦስን ቤተ ሰብ ሁሉ ፈጀ።

13 ይህም የሆነው ባኦስና ልጁ ኤላ፣ በማይረቡ ጣዖቶቻቸው ምክንያት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ በሠሩት ኀጢአት ሁሉና፣ እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ነበር።

14 ሌላው ኤላ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

15 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሆኖ ሰባት ቀን ብቻ ገዛ። በዚህ ጊዜ ሰራዊቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ የሆነችውን ገባቶንን ከቦ ሰፍሮ ነበር።