1 ከብዙ ጊዜ በኋላም በሦስተኛው ዓመት እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ለኤልያስ መጣለት፤ “ሄደህ ለአክዓብ ተገለጥ፤ እኔም በምድሪቱ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ።”
2 ስለዚህም ኤልያስ ራሱን በአክዓብ ፊት ለመግለጥ ሄደ።በዚህ ጊዜ ራብ በሰማርያ ክፋኛ ጸንቶ ነበር።
3 አክዓብም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ አብድዩን ጠራው፤ አብድዩም እግዚአብሔርን በጣም የሚፈራ ሰው ነበር።
4 ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት እያስገደለች በነበረበት ጊዜ፣ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውሃ ይሰጣቸው ነበር።