1 ነገሥት 18:17-23 NASV

17 ኤልያስንም ባየው ጊዜ፤ “እስራኤልን የምታውክ አንተ ነህን?” አለው።

18 ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ።

19 አሁንም ሕዝቡ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲገናኘኝ ለመላው እስራኤል ጥሪ አድርግ። ከኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ አምሳውን የበኣል ነቢያት፣ አራት መቶውንም የአሼራ ነቢያት አምጣቸው።”

20 ስለዚህ አክዓብ በመላው እስራኤል ጥሪ አደረገ፣ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።

21 ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ።ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።

22 ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍሁ እኔ ብቻ ነኝ፤ በኣል ግን አራት መቶ አምሳ ነቢያት አሉት።

23 ሁለት ወይፈኖች ስጡን፤ እነርሱም አንዱን መርጠው ይውሰዱ፤ በየብልቱም ቈራርጠው፣ በዕንጨት ላይ ያኑሩት፤ ግን እሳት አያንድዱበት፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፤ በዕንጨትም ላይ አኖረዋለሁ፤ እሳት አላነድበትም።