2 ስለዚህም ኤልያስ ራሱን በአክዓብ ፊት ለመግለጥ ሄደ።በዚህ ጊዜ ራብ በሰማርያ ክፋኛ ጸንቶ ነበር።
3 አክዓብም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ አብድዩን ጠራው፤ አብድዩም እግዚአብሔርን በጣም የሚፈራ ሰው ነበር።
4 ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት እያስገደለች በነበረበት ጊዜ፣ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውሃ ይሰጣቸው ነበር።
5 አክዓብም አብድዩን፣ “ተነሣና በአገሪቱ ውስጥ ወዳሉት ምንጮችና ሸለቆዎች ሂድ፤ ፈረሶቻችንና በቅሎዎቻችን እንዳይሞቱ በሕይወት እንዲቈዩ ምናልባት ሣር እናገኝ ይሆናል።” አለው።
6 ስለዚህ የሚሄዱበትን ምድር ተከፋፈሉ፤ አክዓብ በአንድ በኩል፣ አብድዩም በሌላ በኩል ሄደ።
7 አብድዩ በመንገድ ላይ ሳለም ኤልያስን አገኘው። አብድዩም ዐወቀው፤ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት፣ “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፤ በእርግጥ አንተ ነህን?” አለው።
8 እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ፤ ሂድና ለጌታህ፣ ‘ኤልያስ እዚሁ አለልህ’ ብለህ ንገረው” ሲል መለሰለት።