1 ነገሥት 18:23-29 NASV

23 ሁለት ወይፈኖች ስጡን፤ እነርሱም አንዱን መርጠው ይውሰዱ፤ በየብልቱም ቈራርጠው፣ በዕንጨት ላይ ያኑሩት፤ ግን እሳት አያንድዱበት፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፤ በዕንጨትም ላይ አኖረዋለሁ፤ እሳት አላነድበትም።

24 ከዚያ እናንተ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶ በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።”ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “ያልኸው መልካም ነው” አሉ።

25 ኤልያስም ለበኣል ነቢያት፣ “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ፤ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ግን እሳት አታንድዱበት” አላቸው።

26 ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የበኣልን ስም ጠሩ፤ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር።

27 እኩለ ቀንም ላይ ኤልያስ፣ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ አምላክ አይደለም እንዴ! ምናልባት በሐሳብ ተውጦ ወይም ሥራ በዝቶበት፣ አልያም በጒዞ ላይ ይሆናል፤ ተኝቶም ከሆነ ቀስቅሱት” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር።

28 ስለዚህ እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር።

29 እኩለ ቀን ዐለፈ፤ እነርሱም የሠርክ መሥዋዕት እስኪቀርብ ድረስ የሚዘላብድ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።