1 ነገሥት 18:31-37 NASV

31 ከዚያም ኤልያስ፣ “ስምህ እስራኤል ይባላል” ተብሎ የእግዚአብሔር ቃል በመጣለት በያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ፤

32 በድንጋዮቹም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ዐሥራ አምስት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጒድጓድ ቈፈረ፤

33 ዕንጨቱን ረበረበ፤ የወይፈኑንም ሥጋ በየብልቱ ከቈረጠ በኋላ በዕንጨቱ ላይ አኖረው። ከዚያም፣ “ውሃ በአራት ጋን ሞልታችሁ፣ በመሥዋዕቱና በዕንጨቱ ላይ አፍስሱ” አላቸው።

34 ደግሞም፣ “እንደ ገና ጨምሩበት” አላቸው፤ እነርሱም ጨመሩበት። “ሦስተኛም ጨምሩበት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ጨመሩበት።

35 ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጒድጓዱንም ሞላው።

36 የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበትም ጊዜ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀረብ ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ።

37 ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።”