1 ነገሥት 2:1-7 NASV

1 ዳዊት የሚሞትበት ጊዜ እንደ ተቃረበም፣ ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤

2 “እነሆ፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ እንግዲህ በርታ፤ ሰውም ሁን።

3 የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የምታደርገው ሁሉ እንዲከናወንልህ፣ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው በመንገዶቹ ተመላለስ፣ ሥርዐቶቹንና ትእዛዛቱን፣ ሕግጋቱንና ደንቦቹን ጠብቅ፤

4 እግዚአብሔርም፣ ‘ዘሮችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፣ እንዲሁም በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው በታማኝነት በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው ከዘርህ አላሳጣህም’ ሲል የሰጠኝን ተስፋ ይፈጽምልኛል።

5 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በእኔ ላይ ያደረገውን፣ እንዲሁም በእስራኤል ሰራዊት አዛዦች በኔር ልጅ በአበኔርና በዬቴሩ ልጅ በአሜሳይ ላይ የፈጸመውን አንተው ራስህ ታውቃለህ፤ ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደማቸውን አፍሶአል፤ በዚህም ደም ወገቡ ላይ የታጠቀውን ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገውን ጫማ በክሎአል።

6 መደረግ ያለበትን በጥበብህ አድርግ፤ ከነሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር እንዲወርድ አታድርግ።

7 “ከወንድምህ ከአቤሴሎም በሸሸሁ ጊዜ መልካም ነገር አድርገውልኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች ግን በጎ ነገር አድርግላቸው፤ ማእድህን ከሚካፈሉ ሰዎችም ጋር አብረው ይብሉ።