10 ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።
11 ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት ባጠቃላይ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።
12 ስለዚህ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ የጸና ሆነ።
13 በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ።
14 ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጒዳይ አለኝ” አላት።እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።
15 እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ።
16 አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት።እርሷም፣ “በል እሺ ተናገር” አለችው።