1 ነገሥት 2:23-29 NASV

23 ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤

24 አሁንም በሚገባ ያጸናኝ፤ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ያስቀመጠኝና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ሥርወ መንግሥትን የመሠረተልኝ ሕያው እግዚአብሔርን አዶንያስ ዛሬ ይሞታል!”

25 ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም አዶንያስን መቶ ገደለው።

26 ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፣ “ሞት የሚገባህ ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፣ አባቴ የተቀበለውንም መከራ ሁሉ አብረኸው ስለ ተቀበልህ፣ እኔ አሁን አልገድልህም፤ ዓናቶት ወዳለው ዕርሻህ ሂድ” አለው።

27 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ዔሊ ቤት በሴሎ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም፣ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አስወገደው።

28 ከአቤሴሎም ጋር ሳይሆን ከአዶንያስ ጋር አሢሮ የነበረው ኢዮአብም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ።

29 ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው።