10 ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።
11 የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።
12 ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።
13 በዚያን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ብዙ ሰራዊት ታያለህን? ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።
14 አክዓብም፣ “ይህን የሚያደርገው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።ነቢዩም፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን የሚያደርጉት የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖች ናቸው’ ” አለው።“ታዲያ ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።ነቢዩም፣ “አንተው ትጀምራለህ” ብሎ መለሰ።
15 ስለዚህ አክዓብ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑትን ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ወጣት መኰንኖች ጠራ፤ ከዚያም የቀሩትን እስራኤላውያን ሰበሰበ፤ እነዚህም በአጠቃላይ ሰባት ሺህ ነበሩ።
16 እነርሱም ቤን ሀዳድና ከእርሱ ጋር ተባብረው የነበሩት ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሰክረው ሳለ እኩለ ቀን ላይ መጡ።