1 ነገሥት 20:25-31 NASV

25 ከእስራኤል ጋር በሜዳው ላይ እንዲጋጠም በፈረሱ ፈንታ ፈረስ፣ በሠረገላው ፈንታ ሠረገላ በመተካት፣ እንደ ተደመሰሰው ያለ ሰራዊት አቋቁም፤ ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ይበልጥ እኛ እንደምንበረታ አያጠራጥርም።” ንጉሡም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማማ፤ እንዳሉትም አደረገ።

26 በተከታዩም የጸደይ ወራት ቤን ሀዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ አፌቅ ወጣ።

27 እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ ሊገጥሟቸው ተሰልፈው ወጡ። ሶርያውያን አገር ምድሩን ሞልተውት ሳለ፣ እስራኤላውያን ግን እንደ ሁለት ትናንሽ የፍየል መንጋ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ሰፈሩ።

28 የእግዚአብሔርም ሰው ወጥቶ ለእስራኤል ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እግዚአብሔር የኰረብታ እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ስፍር ቊጥር የሌለው ሰራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

29 በየሰፈሩበትም ቦታ ሰባት ቀን ከተፋጠጡ በኋላ በሰባተኛው ቀን ጦርነት ገጠሙ። እስራኤላውያንም በአንዲት ጀምበር ከሶርያውያን ሰራዊት መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ።

30 የቀሩት ወደ አፌቅ ከተማ ሸሹ፤ በዚያም በሃያ ሰባቱ ሺህ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤንሀዳድም ወደ ከተማዪቱ ሸሽቶ በመሄድ ወደ አንዲት እልፍኝ ገብቶ ተደበቀ።

31 ሹማምቱም፣ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሓሪዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ አሁንም እንነሣና በወገባችን ላይ ማቅ ታጥቀን፣ በራሳችን ላይ ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንሂድ፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፋት ይሆናል” አሉት።