1 ነገሥት 20:4-10 NASV

4 የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት።

5 መልክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሀዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤

6 ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ”

7 የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።

8 ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት።

9 ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ።

10 ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።