1 ነገሥት

ምዕራፎች 20:6-12

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

6ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ” 7የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው። 8ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት። 9ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ። 10ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ። 11የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። 12ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።