1 ነገሥት 20:7-13 NASV

7 የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።

8 ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት።

9 ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ።

10 ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።

11 የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።

12 ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።

13 በዚያን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ብዙ ሰራዊት ታያለህን? ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።