1 ሰሎሞን የግብፅ ንጉሥ የፈርዖን ወዳጅ ሆነ፤ የፈርዖንንም ልጅ አገባ። እርሱም ቤተ መንግሥቱን፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጥር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አስቀመጣት።
2 በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ስም ገና ቤተ መቅደስ ስላልተሠራ፣ ሕዝቡ አሁንም መሥዋዕት የሚያቀርበው በማምለኪያ ኰረብታ ላይ ነበር።
3 ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ በአባቱ በዳዊት ሥርዐትም ይሄድ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ በኰረብታዎች ላይ መሥዋዕት ይሠዋና ዕጣን ያጥን ነበር።
4 ከሁሉ የሚበልጠው የማምለኪያ ኰረብታ ገባዖን ስለ ነበረ፣ ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰሎሞን በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።