1 ነገሥት 3:4-10 NASV

4 ከሁሉ የሚበልጠው የማምለኪያ ኰረብታ ገባዖን ስለ ነበረ፣ ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰሎሞን በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

5 በገባዖንም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ አምላክም፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምን” አለው።

6 ሰሎሞን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባቴ ዳዊት በእውነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና በፊትህ ስለተመላለሰ፣ ለባሪያህ ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ ይህ ታላቅ ቸርነት እንዲቀጥል በማድረግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተኸዋል።

7 “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም።

8 ባሪያህ አንተ በመረጥኸው ሕዝብ፣ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ታላቅ ሕዝብ መካከል ይገኛል።

9 ስለዚህ መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?”

10 ሰሎሞን ይህን በመለመኑ ጌታ ደስ አለው፤