1 ነገሥት 7:10-16 NASV

10 መሠረቱም ዐሥርና ስምንት ክንድ ርዝመት ባላቸውና ምርጥ በሆኑ ታላላቅ ድንጋዮች የተሠራ ነበር።

11 በላዩም ላይ ምርጥ የሆኑ፣ በልክ በልኩ የተቈረጡ ድንጋዮችና የዝግባ ሳንቃዎች ነበሩ።

12 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ከመመላለሻ በረንዳው ጭምር እንደ ትልቁ አደባባይ አምሮ በተጠረበ ሦስት ረድፍ ድንጋይና ተስተካክሎ በተከረከመ በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ የታጠረ ነበር።

13 ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤

14 የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለ ሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ።

15 ኪራም የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ ዙሪያው ዐሥራ ሁለት ክንድ የሆነ፣ ሁለት የናስ ምሰሶዎች ሠራ።

16 እንዲሁም በምሰሶዎቹ አናት ላይ የሚሆኑ፣ ሁለት ጒልላት ከቀለጠ ናስ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ጒልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበር።