1 ነገሥት 7:13-19 NASV

13 ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤

14 የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለ ሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ።

15 ኪራም የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ ዙሪያው ዐሥራ ሁለት ክንድ የሆነ፣ ሁለት የናስ ምሰሶዎች ሠራ።

16 እንዲሁም በምሰሶዎቹ አናት ላይ የሚሆኑ፣ ሁለት ጒልላት ከቀለጠ ናስ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ጒልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበር።

17 በምሰሶዎቹ አናት ላይ ላሉት ጒልላቶችም ጌጥ እንዲሆኑ፣ ለእያንዳንዳቸው ሰባት የመረብ ሰንሰለት አበጀ፤

18 ደግሞም በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን ጒልላቶች ለማስጌጥ የእያንዳንዱን መረብ ዙሪያ የሚከቡ ሮማኖች በሁለት ረድፍ ሠራ፤ ለሁለቱም ጒልላቶች ያደረገው ተመሳሳይ ነበር።

19 በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጒልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው።