1 ነገሥት 8:21-27 NASV

21 ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”

22 ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣

23 እንዲህ አለ፤“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በፍጹም ልባቸው ጸንተው ለሚኖሩ አገልጋዮችህ ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ጽኑ ፍቅርህን የምትገልጥ አንተ ነህ፤ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እንዳንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤

24 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ ጠብቀሃል፤ በአፍህ ተናገርህ፤ ይህንኑም በዛሬው ዕለት በእጅህ ፈጸምኸው።

25 “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ለአባቴ ለባሪያህ ለዳዊት፣ ‘አንተ እንዳደረግኸው ሁሉ፣ ልጆችህ በፊቴ ለመመላለስ በሚያደርጉት ሁሉ ይጠንቀቁ ብቻ እንጂ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው አታጣም’ ስትል የሰጠኸውን ተስፋ ፈጽምለት።

26 አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።

27 “ነገር ግን አምላክ በእርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምኑ ሊበቃ!