1 ነገሥት 8:28-34 NASV

28 አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህም ሆኖ የባሪያህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ በዛሬው ዕለት ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ልመና አድምጥ።

29 ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወዳልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ።

30 ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ልመናቸውን ተቀበል፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

31 “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ መማል ኖሮበት ቢመጣና በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣

32 ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት።

33 ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣

34 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህ የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሰህ አግባቸው።