11 ንጉሥ ሰሎሞን በገሊላ የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም ሰጠው፤ ንጉሡ ይህን ያደረገውም፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዝግባ፣ ጥድና ወርቅ ኪራም ሰጥቶት ስለ ነበር ነው፤
12 ይሁን እንጂ ኪራም ከጢሮስ ተነሥቶ ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት በሄደ ጊዜ አልተደሰተባቸውም፤
13 እርሱም፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ ከተሞች ምንድን ናቸው?” አለ፤ እነዚህንም ‘ከቡል ምድር’ አላቸው፤ እስከ ዛሬም በዚሁ ስም ይጠራሉ።
14 በዚያን ጊዜ ኪራም ለንጉሡ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ልኮለት ነበር።
15 ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ የራሱን ቤተ መንግሥት፣ ሚሎን፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ሐጾርን፣ መጊዶንና ጌዝርን ለመሥራት የጒልበት ሠራተኞች መልምሎ ነበር።
16 የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ በጌዝር ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ አቃጠላትም፤ ነዋሪዎቿን ከነዓናውያንን ገድሎ ለልጁ ለሰሎሞን ሚስት መዳሪያ አድርጎ ሰጥቶአት ነበር፤
17 ሰሎሞንም ጌዝርን መልሶ ሠራት፤ እንዲሁም የታችኛውን ቤትሖሮንን፣