2 ነገሥት 10:21-27 NASV

21 ከዚያም በመላው እስራኤል መልእክት ላከ፤ የበኣል አገልጋዮች በሙሉ መጡ፤ ማንም አልቀረም፤ ሁሉም ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገቡ፤ የበኣል ቤተ ጣዖት ዳር እስከ ዳር ሞላ።

22 ኢዩም የልብስ ቤቱን ኀላፊ፣ “ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ አልባሳት አውጣ” አለው፤ እርሱም አልባሳቱን አወጣላቸው።

23 ከዚያም ኢዩ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገባ። የበኣልንም አገልጋዮች፣ “እንግዲህ የበኣል አገልጋዮች ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እዚህ አብረዋችሁ አለመኖራቸውን አረጋግጡ” አላቸው።

24 ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ። በዚህ ጊዜም ኢዩ፣ “በእጃችሁ አሳልፌ ከሰጠኋችሁ ሰዎች አንድ እንኳ እንዲያመልጥ ያደረገ በገመዱ ይገባበታል” ብሎ በማስጠንቀቅ ውጭ ሰማንያ ሰዎች አዘጋጅቶ ነበር።

25 ኢዩ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ ጠባቂዎቹንና የጦር አለቆቹን፣ “ግቡና ግደሏቸው፤ ማንም እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ። እነርሱም በሰይፍ ፈጇቸው፤ ጠባቂዎቹና የጦር ሹማምንቱም ሬሳውን በሙሉ ወደ ውጭ አውጥተው ጣሉ። ከዚያም ወደ ውስጠኛው የበኣል ቤተ ጣዖት ገቡ።

26 ከድንጋይ የተሠሩትንም ማምለኪያ ምስሎች ከበኣል ቤተ ጣዖት አውጥተው አቃጠሉ።

27 የበኣልን ማምለኪያ ምስል ቀጠቀጡ፤ የበኣልንም ቤተ አምልኮ አፈረሱ፤ ይህንንም ሕዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ የኵስ መጣያው አድርጎታል።