2 ነገሥት 11:11-17 NASV

11 ወታደሮቹም እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን ይዘው፣ ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።

12 ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጠው፣ መንገሡን ዐወጀ፤ ኢዮአስም ተቀብቶ ነገሠ። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።

13 ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደች።

14 እነሆ፤ በወጒ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀዳ፣ “ይህ ክዳት ነው! ክዳት ነው!” በማለት ጮኸች።

15 ካህኑ ዮዳሄም ጭፍሮቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤ የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ በሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔር ቤት መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር።

16 ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት ስፍራ ስትደርስ፣ ይዘው እዚያው ገደሏት።

17 ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ፤ እንደዚሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን መሠረተ።