13 ለቤተ መቅደሱ ከገባው ገንዘብ ግን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግልጋሎት ለሚውሉ የብር ጽዋዎች፣ መኰስተሪያዎች፣ ድስቶች፣ መለከቶችና ወይም ለሌሎች የወርቅም ሆነ የብር ዕቃዎች መሥሪያ አልዋለም፤
14 የተከፈለው ግን ቤተ መቅደሱን ለሚያድሱ ሠራተኞች ብቻ ነበር።
15 ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘቡ የተሰጣቸው ሰዎች ፍጹም ታማኞች በመሆናቸው ተቈጣጣሪ ማድረግ አላስፈለጋቸውም ነበር።
16 ስለ በደል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበው ገንዘብ ግን የካህናቱ በመሆኑ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይገባም ነበር።
17 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጣ፤ ጌትንም አደጋ ጥሎ ያዛት። ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ፊቱን አዞረ።
18 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ ግን አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮሆራም፣ አካዝያስ ለእግዚአብሔር ቀድሰው የለዩአቸውን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ፣ እርሱ ራሱ የቀደሳቸው ስጦታዎች እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ሰብስቦ ለሶርያ ንጉሥ ለአዛሄል ላከለት፤ አዛሄልም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።
19 ኢዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ተግባርና የፈጸመው ሥራ ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?