2 ነገሥት 14:7-13 NASV

7 የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺህ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው።

8 ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት ይዋጣልን” ሲል መልእክተኞች ላከበት።

9 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ በሚስትነት ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው።

10 በእርግጥ ኤዶምን ድል አድርገሃል፤ ታዲያ ልብህ አለመጠን አይኵራራ። ድል በማድረግህ አትንጠራራ፤ አርፈህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር የራስህንስ፣ የይሁዳንስ ውድቀት ለምን ትሻለህ?”

11 አሜስያስ ግን አልሰማም፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ጦርነት ገጠሙ።

12 ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።

13 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ የሆነውን ቅጥር አፈረሰ።