2 ሲነግሥም ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3 አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ ዓዛርያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።
4 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና እጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
5 እግዚአብሔርም ንጉሡን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ በለምጽ መታው፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያን ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።
6 በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
7 ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
8 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ስድስት ወርም ገዛ።