2 ነገሥት 2:1-6 NASV

1 እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር።

2 ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው፣ እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ ካንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ አብረው ወደ ቤቴል ወረዱ።

3 በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው አውቀሃልን?” አሉት።ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ።

4 ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ።

5 በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት።እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ።

6 ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው።እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም አብረው ሄዱ።