2 ነገሥት 20:7-13 NASV

7 ከዚያም ኢሳይያስ፣ “ትኵስ የበለስ ጥፍጥፍ አዘጋጁ” አላቸው፤ እነርሱም አዘጋጅተው ዕባጩ ላይ አደረጉለት፤ ተፈወሰም።

8 ሕዝቅያስም፣ “እግዚአብሔር እኔን ስለ መፈወሱ፣ ከሦስት ቀን በኋላም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለ መውጣቴ ምልክቱ ምንድን ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀው።

9 ኢሳይያስም፣ “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ምልክቱ ይህ ነው፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይቅደምን? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ?” ሲል ጠየቀው።

10 ሕዝቅያስም መልሶ፣ “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ ይልቁን ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ” አለ።

11 ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አካዝ በሠራው ደረጃ ላይ የወረደውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላው እንዲመለስ አደረገ።

12 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን የሕዝቅያስን መታመም ሰምቶ ስለ ነበር፣ ደብዳቤና ገጸ በረከት ለሕዝቅያስ ላከለት።

13 ሕዝቅያስም መልክተኞቹን ተቀብሎ በዕቃ ቤቱ ያለውን ሁሉ ብሩን፣ ወርቁን ቅመማ ቅመሙንና ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ዘይት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱንና በቀረውም ግምጃ ቤት ያለውን በሙሉ አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በመላው ግዛቱ ሕዝቅያስ ሳያሳያቸው የቀረ ምንም ነገር አልነበረም።