2 ነገሥት 23:30-36 NASV

30 የኢዮስያስም አገልጋዮች ከመጊዶ ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው በገዛ መቃብሩ ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፤ ቀብተውም በአባቱ እግር አነገሡት።

31 ኢዮአክስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሦስት ወር ገዛ። እናቱ አሚጣል ትባላለች፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

32 አባቶቹ እንዳደረጉ ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

33 በኢየሩሳሌም ተቀምጦ እንዳይ ገዛም ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ሪብላ በምትባል ቦታ በሰንሰለት አሰረው፤ በይሁዳም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት።

34 ፈርዖን ኒካዑ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ እግር አነገሠው፤ ኤልያቄም የተባለ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ነገር ግን ኢዮአክስን በምርኮ ወደ ግብፅ ወሰደው፤ እርሱም በዚያ ሞተ።

35 ኢዮአቄምም ፈርዖን ኒካዑ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፤ ይህን ለማድረግም የመሬት ግብር ጣለ፤ የአገሩም ሰዎች እንደ ገቢው መጠን ብሩንና ወርቁን እንዲከፍሉ አደረገ።

36 ኢዮአቄም ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ዘቢዳ ትባላለች፤ እርሷም የሩማ ተወላጅ የፈዳያ ልጅ ነበረች።