2 ነገሥት 25:10-16 NASV

10 በክብር ዘቡ አዛዥ የተመራው መላው የባቢሎን ሰራዊትም በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበረውን ቅጥር አፈረሰው።

11 የክብር ዘቡ አዛዥም በከተማዪቱ ቀርቶ የነበረውን፣ ከድቶም በዚያ የተገኘውን ሰው ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ የገባውን ጭምር በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው።

12 ሆኖም አዛዡ ከአገሬው ሰዎች ምንም የሌላቸውን ድኾች ወይን እንዲተክሉ፣ ዕርሻም እንዲያርሱ እዚያው ተዋቸው።

13 ባቢሎናውያን የናስ ዐምዶቹን፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ክብ በርሜል ሰባብረው ናሱን ወደ ባቢሎን ወሰዱ።

14 እንዲሁም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ጭልፋዎቹን፣ ባጠቃላይም ከናስ የተሠሩትን የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ።

15 የክብር ዘቡ አዛዥም ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ጽናዎችና የመርጫ ወጭቶችን ወሰደ።

16 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ ብሎ ከናስ ያሠራቸው ሁለት ዐምዶች፣ የውሃ ማጠራቀሚያው ክብ በርሜልና ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎቹ ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር።