2 ነገሥት 25:11-17 NASV

11 የክብር ዘቡ አዛዥም በከተማዪቱ ቀርቶ የነበረውን፣ ከድቶም በዚያ የተገኘውን ሰው ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ የገባውን ጭምር በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው።

12 ሆኖም አዛዡ ከአገሬው ሰዎች ምንም የሌላቸውን ድኾች ወይን እንዲተክሉ፣ ዕርሻም እንዲያርሱ እዚያው ተዋቸው።

13 ባቢሎናውያን የናስ ዐምዶቹን፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ክብ በርሜል ሰባብረው ናሱን ወደ ባቢሎን ወሰዱ።

14 እንዲሁም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ጭልፋዎቹን፣ ባጠቃላይም ከናስ የተሠሩትን የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ።

15 የክብር ዘቡ አዛዥም ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ጽናዎችና የመርጫ ወጭቶችን ወሰደ።

16 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ ብሎ ከናስ ያሠራቸው ሁለት ዐምዶች፣ የውሃ ማጠራቀሚያው ክብ በርሜልና ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎቹ ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር።

17 እያንዳንዱ ዐምድ ዐሥራ ስምንት ክንድ ሲሆን፣ የናስ ጒልላት ነበረው፤ የጒልላቱ ርዝመት ሦስት ክንድ ሆኖ፣ ዙሪያውን በሙሉ የናስ መርበብና የሮማን ፍሬዎች ቅርጽ ነበረው፤ ሌላውም ዐምድ ከነቅርጾቹ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነበር።