2 ነገሥት 9:1-6 NASV

1 ነቢዩ ኤልሳዕ ከነቢያት ማኅበር አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ወገብህን ታጥቀህ፣ ይህን የዘይት ማሰሮ በመያዝ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሂድ።

2 በዚያም ስትደርስ የናሜሲን የልጅ ልጅ፣ የኢዮ ሣፍጥን ልጅ ኢዩን ፈልገው። ወደ እርሱም ቀርበህ ከጓደኞቹ ለብቻ ከነጠልኸው በኋላ፣ ወደ እልፍኝ አስገባው።

3 ከዚያም ማሰሮውን ይዘህ ዘይቱን በራሱ ላይ አፍስስና፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እኔ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀባሁህ” ’ ብለህ ዐውጅ። ከዚያም በሩን ከፍተህ ሩጥ፤ ፈጽሞ አትዘግይ።”

4 ስለዚህ ጐልማሳው ነቢይ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሄደ።

5 በዚያ እንደ ደረሰም፣ የሰራዊቱ ጦር መኰንኖች በአንድነት ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “መኰንን ሆይ፤ ወደ አንተ ተልኬአለሁ” አለ።ኢዩም፣ “ለማንኛችን ነው?” ሲል ጠየቀ።እርሱም፣ “መኰንን ሆይ፤ ለአንተ ነው” ብሎ መለሰ።

6 ኢዩም ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ከዚያም ነቢዩ ዘይቱን በኢዩ ላይ አፈሰሰና እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀብቼሃለሁ።