2 ነገሥት 9:12-18 NASV

12 እነርሱም፣ “ይህማ ትክክል አይደለም ይልቅስ እውነቱን ንገረን” አሉት።ኢዩም እንዲህ አለ፤ “እርሱ የነገረኝማ ይህ ነው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ።’ ”

13 ከዚያ ሁሉም ቶሎ ብለው ልብሳቸውን እያወለቁ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ ከዚያም መለከት ነፍተው፣ “ኢዩ ነግሦአል” አሉ።

14 ስለዚህ የናሜሲ የልጅ ልጅ፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ አሤረ። በዚህ ጊዜ ኢዮራምና እስራኤል ሁሉ በሬማት የምትገኘውን ገለዓድን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጥቃት ለማዳን ይጠብቁ ነበር።

15 ንጉሥ ኢዮራም ግን የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን ጦርነት በገጠመው ጊዜ፣ ሶርያውያን ካደረሱበት ቊስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም፣ “እንግዲህ ሐሳባችሁ እንዲህ ከሆነ፣ ይህን ነገር ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ እንዳይናገር፣ ማንም ሰው ከዚህች ከተማ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” አለ።

16 ከዚያም በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ ይህን ያደረገውም ኢዮራም በዚያ ስለተኛና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም እርሱን ለመጠየቅ ወደዚያው ስለወረደ ነው።

17 በኢይዝራኤል ግንብ ማማ ላይ የቆመው ጠባቂ የኢዩ ወታደሮች መቅረባቸውን አይቶ፣ “ኧረ ወታደሮች መጡ” በማለት ጮኾ ተናገረ።ኢዮራምም፣ “አንድ ፈረሰኛ ተጠርቶ፤ እንዲገናኛቸው ላኩትና፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎ ይጠይቅ” ሲል አዘዘ።

18 ፈረሰኛውም ኢዩን ለመገናኘት ጋልቦ ሄደና፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎአል” አለው።ኢዩም፣ “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጒዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ እለፍና ተከተለኝ” አለው።ጠባቂውም፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ብሎ አሳወቀ።