5 በዚያ እንደ ደረሰም፣ የሰራዊቱ ጦር መኰንኖች በአንድነት ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “መኰንን ሆይ፤ ወደ አንተ ተልኬአለሁ” አለ።ኢዩም፣ “ለማንኛችን ነው?” ሲል ጠየቀ።እርሱም፣ “መኰንን ሆይ፤ ለአንተ ነው” ብሎ መለሰ።
6 ኢዩም ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ከዚያም ነቢዩ ዘይቱን በኢዩ ላይ አፈሰሰና እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀብቼሃለሁ።
7 የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ።
8 የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ ባሪያም ይሁን ተወላጅ፣ በእስራኤል የሚገኘውን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ሁሉ ከአክዓብ እቈርጣለሁ።
9 ከእንግዲህ የአክዓብን ቤት፣ እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
10 ኤልዛቤልን ግን በኢይዝራኤል ዕርሻ ውሾች ይበሏታል፤ የሚቀብራትም አይኖርም።’ ” ይህን ተናግሮም መዝጊያውን ከፍቶ ሮጠ።
11 ኢዩ ወጥቶ የጦር አለቆች ወደሆኑት ጓደኞቹ እንደ ደረሰ፣ ከመካከላቸው አንዱ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው? ይህ እብድ ወደ አንተ የመጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ የሚናገረውን እናንተም ታውቃላችሁ” ሲል መለሰ።