2 ዜና መዋዕል 23:12-18 NASV

12 ጎቶልያም የሚሯሯጠውንና ደስታውን ለንጉሡ የሚገልጠውን ሕዝብ ሁካታ ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች።

13 ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዐምዱ አጠገብ ቆሞ አየች፣ የጦር መኮንኖችና መለከት ነፊዎችም በንጉሡ አጠገቡ ነበሩ፤ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይደሰቱ፣ መለከትም ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ ታጅበው የበዓሉን ዝማሬ ይመሩ ነበር፤ ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ ይህ ዐመፅ ነው! ይህ ዐመፅ ነው!” ብላ ጮኸች።

14 ካህኑ ዮዳሄም የወታደር አዛዥ ወደሆኑት ወደ መቶ አለቆቹ፣ “በሰልፉ መካከል አውጥታችሁ አምጧት፤ የሚከተላት ካለም በሰይፍ ግደሉት” ሲል ላከባቸው። ካህኑም፣ “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አትግደሏት” ብሎ ነበርና።

15 እርሷም በቤተ መንግሥቱ ግቢ የፈረስ መግቢያ በር ወደተባለው ቦታ እንደ ደረሰች ያዟት፤ በዚያም ገደሏት።

16 ዮዳሄም ራሱ፣ ሕዝቡና ንጉሡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሚሆኑ ቃል ኪዳን ገባ።

17 ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በሙሉ ሄዶ የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ጣዖታቱን አደቀቀ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።

18 ዮዳሄ በሙሴ ሕግ እንደተጻፈውና ዳዊትም እንዳዘዘው፣ በደስታና በመዝሙር የሚቃጠለውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት ለመደባቸው ካህናትና ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ኀላፊነት ሰጣቸው።