መሳፍንት 11:34-40 NASV

34 ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።

35 ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ “ወይኔ ልጄ ጒድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና” ብሎ በኀዘን ጮኸ።

36 እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለእግዚአብሔር ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን እግዚአብሔር ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ።

37 ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።”

38 እርሱም፣ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ።

39 ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፣

40 የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ኀዘን ያደርጉላታል።