መሳፍንት 16:11-17 NASV

11 እርሱም፣ ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።

12 ደሊላም አዳዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱ ግን ክንዱ የታሰረባቸውን ገመዶች እንደ ፈትል ክር በጣጠሳቸው።

13 ደግሞም ደሊላ ሳምሶንን፣ “እስካሁን አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል። እባክህን አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ንገረኝ” አለችው።እርሱም መልሶ፣ “የራስ ጠጒሬን ሰባት ቈንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጒነሽ በችካል ብትቸክዪው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም መተኛቱን አይታ ሰባቱን ቈንዳላዎቹን ከድር ጋር ጐነጐነችው፤

14 ከችካልም ጋር ቸከለችው።እንደ ገናም፣ “ሳምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ችካሉን ከነድሩ፣ ከነቈንዳላው ነቀለው።

15 ከዚያም፣ “ሳታምነኝ እንዴት ‘እወድሻለሁ’ ትለኛለህ? ስታታልለኝና የኀይልህንም ታላቅነት ምስጢር ስትደብቀኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው” አለችው።

16 በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው።

17 ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆንሁ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጒር ቢላጭ ግን ኀይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።