መሳፍንት 18:15-21 NASV

15 ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት።

16 ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር።

17 ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፣ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን አምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ።

18 እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፣ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው።

19 እነርሱም፣ “ዝም በል! አንዲት ቃል እንዳትተነፍስ፤ ከእኛ ጋር ሁን፤ አባትም ካህንም ሁነን፤ ለአንተስ የአንድ ቤተ ሰብ ካህን ከመሆን ይልቅ በእስራኤል የአንዱ ነገድና ጐሣ ካህን ሆነህ ማገልገሉ አይሻልህምን?” አሉት።

20 ይህም ካህኑን ደስ አሰኘው፤ እርሱም ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና የተቀረጸውን ምስል ይዞ ከሕዝቡ ጋር ሄደ።

21 እነርሱም ሕፃናታቸውን፣ የከብቶቻቸውን መንጋና ሀብታቸውን ሁሉ ወደ ፊት በማስቀደም ተመልሰው ሄዱ።