17 ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማዪቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፣ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።
18 ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተ ልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም።
19 ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፣ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።”
20 ሽማግሌውም፣ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደሩ” አለው።
21 ስለዚህ ወደ ቤቱ አስገብቶት ለአህዮቹ ገፈራ ሰጣቸው፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፤ ጠጡም።
22 በግብዣው ላይ እየተደሰቱ ሳለ፣ ጥቂት የከተማዪቱ ወስላቶች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም እየደበደቡ፣ “ዝሙት እንድንፈጽምበት ቤትህ የገባውን ሰው አውጣው” በማለት የቤቱ ባለቤት በሆነው ሽማግሌ ላይ ጮኹበት።
23 የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።