8 ከዚያም ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመነሣት እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም፤ ማንኛችንም ወደ ቤታችን አንመለስም።
9 ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፤ በዕጣው መሠረት እንዘምትበታለን።
10 ከመላው የእስራኤል ነገዶችም ለሰራዊቱ ስንቅ እንዲይዙ፣ ከመቶው ዐሥር፣ ከሺው አንድ መቶ፣ ከዐሥር ሺው ደግሞ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን። ከዚያም ሰራዊቱ በብንያም ወደምትገኘው ጊብዓ በሚደርስበት ጊዜ፣ ነዋሪዎችዋ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።”
11 ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመተባበር በከተማዪቱ ላይ ዘመቱባት።
12 የእስራኤል ነገዶች ለመላው የብንያም ነገድ እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላኩ፣ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ክፉ ድርጊት ምንድ ነው?
13 አሁንም እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ድርጊት ከእስራኤል እንድናስወግድ፣ እነዚያን የጊብዓን ወስላቶች አሳልፋችሁ ስጡን።”ብንያማውያን ግን ወገኖቻቸውን እስራኤላውያንን አልሰሟቸውም ነበር፤
14 ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ።