መሳፍንት 21:1-7 NASV

1 እስራኤላውያን በምጽጳ፣ “ከእኛ አንድም ሰው ሴት ልጁን በጋብቻ ለብንያማውያን መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር።

2 ሕዝቡ ወደ ቤቴል ሄደው በዚያም እስከ ማታ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ አምርረው አለቀሱ፤

3 እንዲህም አሉ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ ለምን በእስራኤል ላይ ሆነ? ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዴት ይታጣ?”

4 በማግሥቱ ጠዋት ሕዝቡ መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ።

5 በምጽጳ፣ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ያልተገኘ ማንኛውም ሰው መገደል አለበት ብለው እስራኤላውያን ተማምለው ስለ ነበር፣ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን አለ?” ሲሉ ጠየቁ።

6 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያማውያን በማዘን እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ታጥቷል፤

7 ሴቶች ልጆቻችንን ለእነዚህ ብንያማውያን በጋብቻ ላንሰጥ በእግዚአብሔር ስለ ማልን ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝላቸው እንችላለን?”