22 የሦስት መቶው ቀንደ መለከት ድምፅ እንደተሰማም እግዚአብሔር በሰፈሩ ውስጥ ያለው ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሰራዊቱ በጽሬራ አቅጣጫ ወደ ቤት ሺጣ፣ ከዚያም አልፈው በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤላሞሖላ ድንበር ድረስ ሸሽተው ሄዱ።
23 በንፍታሌም፣ በአሴርና በመላው የምናሴ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ተጠርተው ወጡ፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ።
24 ጌዴዎንም በኤፍሬም ኰረብታማ አገር ለሚኖሩት ሁሉ፣ “በምድያማውያን ላይ ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስ ወንዝ ቀድማችሁ ያዙ” አላቸው።ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጡ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስን ወንዝ ያዙ።
25 እንዲሁም ሔሬብና ዜብ የተባሉትን ሁለቱን የምድያም መሪዎች ያዙ። ሔሬብን በሔሬብ ዐለት አጠገብ፣ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሏቸው፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብን ራስ ቈርጠው ጌዴዎን ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ይዘው መጡ።