መሳፍንት 9:44-50 NASV

44 ከዚያም አቤሜሌክና አብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፣ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው።

45 በዚያን ዕለት አቤሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማዪቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማዪቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት።

46 በሴኬም ግምብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይህን እንደ ሰሙ፤ በኤልበሪት ቤተ መቅደስ ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገቡ።

47 አቤሜሌክም በዚያ መመሸጋቸውን ሲሰማ፣

48 እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውም ላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፣ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው።

49 ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቤሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ምሽግ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።

50 ከዚያም አቤሜሌክ ወደ ቴመስ በመሄድ ከተማዪቱን ከቦ ያዛት።