መሳፍንት 9:48-54 NASV

48 እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውም ላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፣ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው።

49 ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቤሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ምሽግ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።

50 ከዚያም አቤሜሌክ ወደ ቴመስ በመሄድ ከተማዪቱን ከቦ ያዛት።

51 ሆኖም በከተማይቱ ውስጥ ብርቱ ግንብ ስለ ነበር፣ የከተማዪቱ ሕዝብ በሙሉ ወንድ ሴት ሳይባል ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በውስጥ ዘግተው ወደ ግንቡ ጣሪያ ወጡ።

52 አቤሜሌክም ተዋግቶ ግንቡን ያዘ፤ ይሁን እንጂ እሳት ለመለኮስ ወደ ግንቡ መግቢያ አጠገብ እንደ ደረሰ፣

53 አንዲት ሴት ከላይ የወፍጮ መጅ በራሱ ላይ ለቀቀችበት፤ ጭንቅላቱንም አፈረሰችው።

54 ወዲያውም ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፣ “ ‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉ እባክህ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው። ስለዚህ አገልጋዩ ወጋው፤ እርሱም ሞተ።